“ቅርጫ አባቶቻችን የሠሩልን አንዱ የማኅበራዊ ግንኙነት ማጠናከሪያ በመኾኑ ልንጠቀምበትና ልንጠብቀው ይገባል” የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 27/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በዓላት ጊዜያቸዉን ጠብቀው ሲመጡ ከሃይማኖታዊ ይዘታቸው በተጨማሪ የሚኖራቸው ማኅበራዊ መስተጋብር ከፍተኛ ነው።
አብሮ መብላትና መጠጣት፣ መጫወት፣ ዘመድ መጠየቅና ሌሎች በዓል በዓል የሚሸቱ ድርጊቶችን መፈጸም በዓላትን የበለጠ ተናፋቂ ያደርጋቸዋል።
በበዓል ወቅት ከሚስተዋሉ ማኅበራዊ ግንኙነቶች ውስጥ አንዱ ቅርጫ ነው። ቅርጫ ሰንጋ፣ በግ ወይም ፍየልን በጋራ መግዛት እና እርድ ከተፈጸመ በኋላም የመከፋፈል ሂደት ነው።
ታዲያ ቅርጫ ሲታሰብ እርስ በእርስ ተፈላልጎ ከመሰባሰብ ጀምሮ እስከ ሥጋ ክፍፍል ድረስ ያለው ሂደት ጥሎት የሚያልፈው ትዝታ ሁሌም በዓል በኖረ የሚያስብል ነው።
ቅርጫን ከበዓላት ውጭ ማድረግ ቢቻልም በበዓል ወቅት የሚደረገው ቅርጫ ከባሕላዊ አለባበስ ጀምሮ ያለው ድባብ ልዩ ያደርገዋል።
የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ የሆነው ወጣት ሽሽጉ እንዳለው ሁሌም በዓል ከመምጣቱ አስቀድሞ በየሳምንቱ ቅርጫን ታሳቢ ያደረገ ገንዘብ እንደሚያስቀምጥ ተናግሯል።
በቅርጫ ምክንያት በርካታ ወዳጆችን ማፍራት እንደቻለም ወጣቱ ተናግሯል።
“ቅርጫ አባቶቻችን ትተውልን የሄዱት አንዱ የማኅበራዊ ግንኙነት ማጠናከሪያ በመኾኑ ልንጠቀምበትና ልንጠብቀው ይገባል” ብሏል።
አቶ ወርቁ አራጌ እንዳሉት ደግሞ ቅርጫ ማኅበራዊ ግንኙነትን ከማዳበር ባለፈ በተለይ አነስተኛ ገቢ ለሚያገኙ ወገኖች ጠቃሚ ነው ብለዋል።
በቅርጫ ወቅት ሁሉም አቅሙ በፈቀደው ልክ ሊከፋፈል እንደሚችልም ነው አቶ ወርቁ የተናገሩት።
ወይዘሮ ዘውድዓለም ወረታው እንደነገሩን በተለይ የኑሮው ውድነት በተባባሰበት ወቅት ቅርጫ መፍትሔ ነው፤ ቅርጫ ማኅበራዊ ግንኙነትን ከማዳበር በዘለለ በተመጣጠኝ ዋጋ የተሻለ ሥጋ እንዲገኝ ያስችላልም ነው ያሉት።
በመጪው የክርስቶስ ልደት በዓል ቅርጫ ለመግባት በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን የተናገሩት መቶ ዓለቃ ደግአረገ ፈንቴ የተባሉ ነዋሪ ናቸው።
ነዋሪው እንዳሉት በዓላት ሲመጡ የቅርጫ ጓደኞቻቸውን ማፈላለግ ግዴታ ነው።
“እርስ በእርስ በመደዋወል ስንት ብር እናዘጋጅ? ስንት ኾነን ነው የምንካፈለው? ከብቱንስ መቸና የት እንግዛው?…መባባሉ ቅርጫን ተናፋቂና ተጠባቂ ያደርገዋል” ብለዋል።
ለቅርጫው ሂደት ብር ሰብሳቢና አስተባባሪ በአባላቱ እንደሚመረጥም መቶ ዓለቃ ደጋረገ አስረድተዋል። በቅርጫ ወቅት ያለው ጭውውትና የሽማግሌዎች ምርቃት ተወዳጅና ተናፋቂ ነውም ነው ያሉት።
Reviews
There are no reviews yet.